Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሰላምን በማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል ይገባል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ሰላምን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ አሳሰቡ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ የአስፈፃሚ አካላትን የ12 ወራት አፈጻጸም ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅትእ እንደገለፁት÷ ባለፉት 12 ወራት የክልሉ ሰላም የተረጋጋ እንዲሆን ውይይቶችና ኮንፈረንሶች ተካሂደዋል።

በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ በተካሄደዉ ክልላዊ የሰላም ኮንፈረንስ በብሔረሰቦች መካከል ተፈጠሮ የነበረውን ግጭት በባህላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓት እና በሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈታ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ጋር በተደረሰው የጋራ ስምምነት መሠረት በጋራ የአስተዳደር ወሰን አካባቢና ወሰን ተሻግረው የሚከሰቱ ግጭቶች እንዲፈቱ በርካታ ስራዎቸ መከናወናቸው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም በአኝዋሃ ብሔረሰብ ዞን ዲማ ወረዳ እና በቤንች ሸኮ ዞን በቤሮና በጉራፈርዳ ወረዳዎች መካከል የተከሰቱ ችግሮችን ከሁለቱ ክልሎች አመራሮች ጋር በመሆን መፍታት መቻሉን እና በአካባቢው የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሮች ለክልሉ ሰላም መደፍረስ አደጋ በመሆናቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ይተላለፉባቸዋል ተብሎ በሚጠረጠሩ ቦታዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉንም  ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ሰላምን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version