አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያን ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው ለመንገድ ደህንነት፣ ለትራፊክ አደጋ እና ለትራንስፖርት ፍሰቱ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በከተማዋ የትራፊክ አደጋን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል የተባለው የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥር የሚገኙ የአንበሳ ከተማ አውቶብስ እና የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያው ገጥመው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማትም በማስገጠም ላይ ይገኛሉ ተብሏል ተገልጿል፡፡
በቀጣይም የአሰራር ሥርዓት መመሪያን በማዘጋጀትና የአፈጻጸም ሲስተሞችን በመዘርጋት የንግድ ትራንስፖርት እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡
ተግባራዊ የሚደረገው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ የተቀናጀ የተሽከርካሪ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ጋር የተጣመረ ሆኖ እንደተሽከርካሪው ሁኔታ ወደ ሞተሩ የሚገባውን ነዳጅ ወይም አየር በመቀነስ የተሽከርካሪው ፍጥነት በሕግ ከተደነገገው በላይ እንዳይፈጥን የሚቆጣጠር መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
መሣሪያው ከኔትዎርክ ውጭ (offline) ሆኖ የሚሰራና ኔትዎርክ ሲያገኝ መረጃዎቹን ወዲያውኑ የሚያስተላልፍና ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ሲታከልበት ከመረጃ ቋት ከያዘው ኮምፒውተር ጋር በመረጃ መረብ ተገናኝቶ የሚናበብና መረጃ የሚያስተላልፍ ቴክኖሎጂ ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡
እንዲሁም አሽከርካሪው ከተቀመጠለት ፍጥነት በላይ ወይም በታች በሚያሽከረክርበት ጊዜ መሣሪያው ለአሽከርካሪው በምልክት ያስጠነቅቃል፤ መረጃውንም ወደ ኤጀንሲው መረጃ ማዕከል ያስተላልፋል፡፡
አሁን እየተዘጋጀ ያለው መመሪያ በማድረግ በከተማ በሰዓት ከ15 እስከ 70 ኪሜ አማካኝ ፍጥነት ወሰን ውስጥ የሚሽከረከር ሲሆን፣ ከከተማ ውጭ ሲሽከረከር መሣሪያው ከሳተላይት በሚመጣለት መረጃ በሚፈቀድለት የፍጥነት ወሰን ራሱን ያስተካክላል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ356 ሰዎች በላይ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ሲያልፍ 1 ሺህ 200 ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

