Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ግብጽ የሃገሪቱ የሚዲያ አውታሮች ስለ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይዘግቡ እገዳ ጣለች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብጽ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የሃገሪቱ የሚዲያ አውታሮች ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ስለ ኮሮና ቫይረስ፣ በሊቢያ እና በሲና በረሃ ከታጣቂዎች ጋር ስላለው ግጭት እንዳይዘግቡ እገዳ ጣለ።

ምክር ቤቱ የሚዲያ አውታሮች በሃገሪቱ ባለስልጣናት የሚወጡ መግለጫዎችን ብቻ እንዲጠቀሙም አስጠንቅቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የሚዲያ አውታሮቹ ስለ ህዳሴው ግድብም ሆነ ክልከላ በተጣለባቸው ጉዳዮች ላይ ማወያየትም ሆነ ዘገባ መስራት አይችሉም ነው የተባለው።

ይህን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይም እርምጃ ይወሰዳል ነው ያለው ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ።

በተጨማሪም የህትመት ሚዲያዎች ክልከላ በተጣለባቸው ጉዳዮች ላይ መስራት የፈለጉትን ዘገባ ከማሳተማቸው በፊት ለሚመለከተው የመንግስት አካል ማስገምገም እና ፈቃድ ማግኘት አለባቸውም ነው ያለው።

የወጣውን ክልከላ ተከትሎም በርካታ የሃገሬው ዜጎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን በተለይም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ድርጊቱን መረጃን ከዜጎች ለመደበቅ ያለመና ነጻነትን የሚጋፋና በሚል ተችተውታል።

ምክር ቤቱ አሁን ላይ ሃገሪቱ ደህንነቷን ለማስጠበቅና ለማረጋገጥ ጠንካራና የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅበት አደገኛና ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን በመግለጫው አመላከቷል።

ምንጭ፦ middleeasteye.net/

Exit mobile version