Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ሚኒስቴር ለኬሚካል ርጭት እንዲውሉ የተገዙት 5 አውሮፕላኖች ተጨማሪ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የናሽናል ኤርዌይስ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

አውሮፕላኖቹ ካላቸው ከፍተኛ አቅም አኳያ በሚኖራቸው ትርፍ ጊዜ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ስራ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ይህም ለአውሮፕላኖቹ አስተዳደር በየዓመቱ መንግስት የሚያወጣውን የወጪ ጫና በመቀነስ ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት አዎንታዊ ሚና እንዳለው ነው የተገለጸው፡፡

በመሆኑም የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአውሮፕላኖቹን አስተዳደር አገልግሎት እየሰጠ ካለው ናሽናል ኤርዌይስ ጋር አውሮፕላኖቹ ወደ ሥራ በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ተፈራርሟል፡፡

የናሽናል ኤርዌይስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኝ ብሩ÷ አውሮፕላኖች በትርፍ ጊዜያቸው ተጨማሪ ሥራ በሀገር ውስጥና በውጭ እንዲሰሩ በማድረግ የራሳቸውን ገቢ እያመነጩ ማስተዳደር ያስፈልጋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አውሮፕላኖቹን በሀገር ውሥጥና ከሀገር ውጭ ለሚመጡ የተለያዩ ሥራዎች ማለትም ለማዕድን ፍለጋ፣ ለሰርቪላንስና መሰል ሥራዎች ናሽናል ኤርዌይስ የኪራይ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ምርጥ ዘርና የደን ውጤቶች አቅርቦት ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ወ/ስላሴ በበኩላቸው÷ በየጊዜው በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ ማሳ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን የበረሃ አንበጣ፣ የግሪሳ ወፍ፣ ተምች እና ሌሎች መደበኛና መደበኛ ያለልሆኑ ተባዮች እና የደን ቃጠሎን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አውሮፕላኖች ከመንግስት በተደረገ ድጋፍ ተገዝተው በሥራ ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

Exit mobile version