አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ቤተሰቦች የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር አካሄደ።
ኤጀንሲው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ለሚገኙ አንድ መቶ አባወራና እማወራዎች ለእያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ ለአንድ ወር አስቤዛ ሊሆናቸው የሚችል ድጋፍ አድርጓል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ÷ ትብብርን በሚጠይቅ በእንደዚህ አይነት ወቅት ኤጀንሲው ይህንን የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ማድረግ መቻሉ የሚጠበቅና ህዝባዊ ተቋሙ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ማዕድ የማጋራት መርሀ ግብሩ በተቋሙ ያሉ ሰራተኞች ከሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ ላይ ተቆራጭ በማድረግ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኤጀንሲው የሴቶች እና ህፃናት ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ፅጌሬዳ ወርቁ÷ ኤጀንሲው ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንፃር ወላጅ ያጡ ህፃናትን እያስተማረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በቀጣይም የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብሩ ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመው ÷በድጋፉ ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎች በኮቪድ 19 ምክንያት የገቢ ምንጫቸው መቋረጡን አንስተዋል።
ሃላፊዋ አያይዘውም በዚህ ፈታኝ ጊዜ እንደዚህ አይነት ድጋፍ ማግኘታቸው አጋር እንዳለ እንዲሰማቸው ያደርጋል ማለታቸውን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

