Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የታችኛው አዋሽ የጎርፍ መከላከል ሥራ ከ70 በመቶ በላይ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በታችኛው አዋሽ አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች የተጀመረው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በታችኛው አዋሽ አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች እየተከናወነ የሚገኘው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ ሒደት በዛሬው ዕለት ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ የአዋሽ ወንዝ ሙላት የሚደርሰውን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም መሰረት በታችኛው፣ በላይኛውና መካከለኛው አዋሽ በ521 ሚሊየን ብር ወጪ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በታችኛው አዋሽ አሳይታና አፋምቦ አካባቢዎችም በ16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ ከ90 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ አፈጻጸሙ 70 በመቶ በላይ መድረሱን ነው የገለጹት።

የቅድመ መከላከል ስራው ሲጠናቀቅ በአካባቢው በአዋሽ ወንዝ ሙላት ሊከሰት የሚችልን አደጋ ለመቀነስ ያስችላል ነው ያሉት።

ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከጎርፍ ሥጋት እንደሚከላከልና መሬቱን ከጉዳት እንደሚታደግም ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በሥራ ሒደቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከወረዳዎቹ አመራሮች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የመከላከል ሥራውን በተያዘለት የሁለት ወር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።

የወረዳዎቹ አመራሮች በበኩላቸው የተጀመረው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራው ጠቀሜታው ጉልህ መሆኑን መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

Exit mobile version