Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን ሰላም ለመጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በሥራ አፈፃፀማቸዉ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ለልዩ የፀረ-ሽብር መምሪያ አመራርና አባላት የምስጋና እና የዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ÷ ልዩ የፀረ-ሽብር መምሪያ አመራርና አባላት በጥብቅ ዲሲፕሊን በመመራት በማንኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በድል መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ልዩ የፀረ-ሽብር ኃይል የፌደራል ፖሊስ ሪፎርምን መሠረት በማድረግ ከዘር፣ ከፖለቲካ፣ ከሐይማኖት ወገንተኝነት እና ከሌብነት የፀዳ ሆኖ የተደራጀ ኃይል መሆኑንና በተሰማራበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ሀገራዊ ተልዕኮውን በጀግንነት የፈፀመ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን የፖሊስ ኃይል ነው ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው÷ የልዩ ፀረ-ሽብር መምሪያ የገጠሙንን የፀጥታ ችግሮች በጀግንነትና በቆራጥነት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የኢትዮጵያን ሰላምና ህልውና ያፀና ታላቅና ልዩ የስራ ክፍል ነው ብለዋል፡፡

Exit mobile version