አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከብሪታንያ አምባሳደር ዳረን ወች ጋር የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በይበልጥ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ፣ በንግድ ድርድሮች እና በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ላይ መክረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለወጪ ንግድና አጠቃላይ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ያለውን ፋይዳ ያብራሩት ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና እና በዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር የደረሰችበትን ምዕራፍ አስረድተዋል፡፡
በንግድ እንቅስቃሴው ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
አምባሳደሩ በበኩከላቸው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማሻሻያና በአኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና የደረሰችበትን ደረጃ አድንቀው÷ በንግድና ኢንቨስትመንት በይበልጥ በመሳተፍ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሠራ አረጋግጠዋል፡፡