አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) “የብልፅግና ፓርቲ መመስረት ኢትዮጵያን ከመበታተን ስጋት የታደገና የህዝቦችን አብሮነት ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን የቀድሞው የብአዴን ኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ከበደ ጫኔ ተናገሩ።
አቶ ከበደ እንዳሉት በኢህአዴግ ምክንያት አጋጥሞ የነበረው የሀገራዊ ስሜት መዳከምና የብሄርተኝነት ፅንፍ ሀገሪቱን የመበታተን አደጋ ላይ ጥሏት ቆይቷል።
ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ይስተዋል የነበረው የሰላም እጦትና አለመረጋጋትም የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የብሄር ፖለቲካው በፅንፍ ሲሰበክ መቀየቱ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በራሱ ብሄራዊ ድርጅቶች ላይ ብቻ ተወስኖ አገር መምራቱም ሌላው ችግር ነበር ነው ያሉት።
ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ ሌብነትና ብልሹ አሰራር እየገነገነ እንዲሄድ በማድርጉ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት ከልክ በማለፉ ችግሩን አወሳስቦት ቆይቷል።
አገራዊ ፓርቲን እውን በማድርግ የጋራ መፍትሄዎችን ለመሻት ኢህአዴግ አንድ ሃገራዊ መሰረት ያለው ፓርቲ እንዲቋቋምና ብሄራዊ ድርጅቶች እንዲፈርሱ ማደረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም ሳይተገበር መቆየቱን ተናግረዋል።
በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ግን ህብረ ብሄራዊዩ ብልፅግና ፓርቲ እውን በመሆኑ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ መታደጉን አቶ ከበደ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የነበረው የተዛባ የፖለቲካ አካሄድ የፈጠረው ችግር የማያባራ ግጭትና መከፋፈል ማስከተሉን አቶ ከበደ አስታውሰዋል።
በአገሪቱ የለውጡ እውን መሆንና የብልፅግና ፓርቲ መመስረትን ተከትሎ አሁን ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም አገራዊ አንድነት ቦታ እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ከአገር ቤትም ይሁን በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎችም ኢትዮጵያዊነታቸውን እንዲያቀነቅኑና ሃገራዊ የገፅታ ግንባታ በመፍጠር ሂደት አበረታች ሁኔታዎች መታየታቸውን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ከበደ ገለፃ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በታቀደው መጠን የኢኮኖሚ እድገት ባይመዘገብም የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ግን ለአገሪቱ ቀጣይ እድገት መሰረት የሚጥሉ ናቸው።
በተለይም የህዳሴው ግድብን ጨምሮ ተቋርጠውና የአሰራር ክፍተት ታይቶባቸው የነበሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ተስተካክለው እንዲቀጥሉ በማድርግ ስኬታማ ስራ ተከናውኗል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ያለውን ትስስርና ትብብር በማስፋትና በማጠንከርም አበረታች ተግባራት መፈፀማቸውን አብራርተዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዘናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

