አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ መደበኛ ስፔሻላይዝድ የጤና፣ ስነ-ምግብ፣ ህዝብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
“ጤናን ማዳበር በአፍሪካ፣ ሁለንተናዊ የጤና፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የህዝብ ቁጥር፣ የመድኃኒት ቁጥጥር፣ ወንጀል መከላከል እና ትምህርት” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ውይይት ላይ 32 ሀገራት ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ ከአፍሪካ የልማት አጀንዳ ጋር በማጣጣም ከጤና፣ ከሥነ-ምግብ፣ ከሕዝብ እና ከመድኃኒት ቁጥጥር ጋር የተያያዙ በርካታ የሥራ ሰነዶችን ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኮንፈረንሱ ከ32 ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች እና ልዑካን ቡድኖች የተገኙ ሲሆን÷ የተለያዩ የአፍሪካ ህብረት አካላት እና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ ሃላፊዎችና ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ በኩል የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማን ጨምሮ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡