አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጽያ አየር መንገድ አዲስ ለሚያስገነባው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የዲዛይን ሥራ ለማሰራት ‘ዳር’ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና የዳር ኩባንያ በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ኡጋንዳ የስራ ሃላፊ ታሪክ አል ካኒ ፈርመዋል።
ስምምነቱ በቢሾፍቱ አቅራቢያ አቡሴራ በተባለ አካባቢ ለሚገነባው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የዲዛይን ሥራውን ማጠናቀቅ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ኩባንያው ከዲዛይን ሥራው በተጨማሪ የግንባታውን ኮንትራክተር መረጣ ላይ የማማከር ሥራ እንደሚሰራም ተገልጿል።
ግንባታው በ5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን÷ በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊየን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚገነባ ተጠቁሟል፡፡
በ2ኛው ምዕራፍ የሚገነባው ደግሞ 100 ሚሊየን ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ነው የተመላከተው፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ እስከ 6 ቢሊየን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልገው የተገለጸ ሲሆን÷ ወጪውም በብድር እንደሚሸፈን በስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ 2 ሺህ 500 የሚሆኑ አባወራዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ለተነሺዎቹ ምትክ ቦታ ተወስዶ የመልሶ ማቋቋሚያ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተነግሯል።
ታሪክ አል ካኒ የሚዘጋጀው ዲዛይን የኢትዮጵያን ብዝሃ ባህል እና ታሪክ ባማከለ መልኩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተያዘለት ጊዜ ተዘጋጅቶ ርክክብ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር በፈጣን ባቡር እና በመኪና መንገድ የሚገናኝበት ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በዘመን በየነ