Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

32ኛው የትግራይ ሰማዕታት ቀን በመቐለ ከተማ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 32ኛው የትግራይ ሰማዕታት ቀን በመቐለ ከተማ ሰማዕታት ሃውልት ቅጥር ጊቢ ተከበረ።

ቀኑ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚኣብሄር፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልል አፈ ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሽፋረ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የተከበረው።

የትግራይ አካል ጉዳተኞች ማህበር ተወካዮች፣ የትግራይ ታጋዮች ማህበር፣ የትግራይ የሰማዕታት ልጆች ማህበር፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል።

ሰማዕታትን በመዘከር የተጀመረው ስነ-ስርዓት ለቀኑ የተዘጋጀ ችቦ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከተለኮሰ በኋላ የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ስነ ስርዓትም ተካሄዷል።

ዶክተር ደብረፅዮን ሰኔ 15ን ስንዘክር ህዝቡ እንዲያልፍለት፣ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት እንዲላቀቅ፣ ከጭቆና እና ግፍ ተላቆ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲያገኝ ብለው ያለፉ ጀግኖች ሰማዕታትን በማስታወስ መሆን ይገባዋል ብለዋል።

ሰማዕታት ብዙ መከራ አሳልፈውና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ገንብተዋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ሰማዕታቱ የአላማ ሰዎች እንደነበሩና ከራሳቸው በላይ የሚያዩት ህዝብ እንደነበራቸው አውስተዋል።

እነሱ የወደቁለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ የአሁኑ ትውልድ አደራ እንደሆነም ገልፀዋል።

የትግራይ ሰማዕታት ቀን “የተሰው ጀግኖችን አደራ በመጠበቅ እንመክታለን” በሚል መሪቃል መከበሩን ከትግራይ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version