አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ከተማና በወረዳው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃያት ካሚልን ጨምሮ ሚኒስትር ዴዔታዎችና የተጠሪ ተቋማት ዋና ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሚስኪ መሐመድና ሌሎች የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራር አካላትና የሥራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
በመርሐ ግብሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በባቢሌ ወረዳ ኢፋና ጃለሌ ቀበሌ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተሻሻሉ የሙዝ ችግኞችን ተክለዋል።
ሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት፣ የሞዴል ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድጋይ የማስቀመጥ ሥራ ያከናውናሉ።
በተጨማሪም በከተማው በሥራ እድል ፈጠራ የተሰማሩ ወጣቶችን የስራ እንቅስቃሴ እንደሚጎበኙ ተመላክቷል፡፡