Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሒደት ላይ ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ መነቃቃት እየተካሄደ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ።

ሚኒስትሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ዳግም የተጀመረው የፕሮጀክቱ የግንባታ ሒደት ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

አቶ መላኩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት÷ የፕሮጀክቱ ዳግም መጀመር የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት በመፍታት ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

ጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ልማቷን የሚያፋጥን ፕሮጀክቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት መንግስት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዲስ ተቋራጭ የተጀመረው የግድቡ ግንባታ በጥሩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ጠቁመው÷ተቋራጩ ግንባታውን በፍጥነትና በጥራት እንዲያጠናቅቅ ተገቢ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ማስገንዝባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጎንደር ከተማ ም/ ከንቲባ ወ/ሮ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው÷ የፌዴራልና የአማራ ክልል አመራር አባላት የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ክትትል ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።

Exit mobile version