Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከግብፅ የሚሰነዘሩ ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎችን ለመመከት ኢትዮጵያዊያን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአዎንታ የሚታይ ነው -ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከግብፅ የሚሰነዘሩ ሀሰተኛ ዜናዎችና ፕሮፖጋንዳዎችን ለመመከት ኢትዮጵያዊያን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአዎንታ የሚታይ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የደብረማርቆስ፣ የዲላና የወሎ ዩኒቨርስቲዎች የህግና የጋዜጠኝነት ምሁራን ÷ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴዎች በሀሰተኛ መረጃ ዓለም የተዛባ ምስል እንዲይዝ የሚጥሩትን ግብፆችን ጥረት ፉርሽ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።

የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ዓለም ዓቀፍ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ግርማው አሸብር÷ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በበዳይነት በተቀረው ዓለም ለመሳል ጥረቶችን ማድረጋቸውን ገልፀው ፣ ኢትዮጵያዊያን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይህንን ጥረት የተገዳደረ ነው ብለዋል።

በዲላ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኬሽን መምህሩ አያሌው ደጀን  በበኩላቸው÷ሀሰተኛ መረጃዎችን በመፈብረክ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የግብፅ መንግስትና መገናኛ ብዙሃን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተለይም አህራም ኦንላይን፣ ኢጅፕት ኢንዲፔንደንት፣ ኢጅፕት ኒውስ ቱደይና ሌሎቹ ይህንን የተፈበረከ ዜና በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ  ሲሆን÷ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን አስተያየቶችና ኮሜንቶችን በመስጠት ኢትዮጵያዊያን እየመሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በብሔራዊ ጥቅማቸው በአንድነት የሚቆሙ ናቸው ያሉት በወሎ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህሩ እጩ ዶክተር ደጀን የማነ  ናቸው።

ምሁሩ አያይዘውም በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረገው እንቅስቃሴ ግን በእውቀት ሊመራ እንደሚገባ ጠቁመው÷ የሚሰጡ አስተያየቶች ከስሜት ይልቅ ስሌትን የኢትዮጵያን ጥቅምም ማሰብ አለባቸው ብለዋል።

በዚህም መንግስት ለህዝቡ መረጃዎችን በመስጠት ዜጎችን በእውቀት  ሊያስታጥቅ ይገባል ነው ያሉት።

ማህበራዊ ሚዲያው ከመደበኛው መገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን ይወስዳል ያሉት ምሁራኑ መገናኛ ብዙሃኑ ተከታታይና ወቅታዊ ዘገባዎችን ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version