አዲስ አበባ ፣ሰኔ 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በ2013 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅት ላይ ተወያይቷል።
በውይይቱም የበጀት ዝግጅቱን አስመልክቶ በገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ዶክትር እዮብ በዘህ ወቅት እንደገለጹት የ2013 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ሲዘጋጅ የ2012 ዓ.ም የበጀት አፈጻጸም ግምገማ ከመካሄዱም ባለፈ የኮረና ወረርሽኝ ተጽዕኖ ታሳቢ ተደርጎ በቅርብ ጊዜያት በአገራችን በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኙ ድሎችን ለማስጠበቅ ታስቦ የታቀደ በጀት ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለካፒታል እና ለብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት ድጋፍ እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማጠናከሪያ በጥቅሉ 476 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸው÷ ከዚህ ውስጥ 350 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከዕርዳታ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት፡፡
አያይዘውም ለ2013 በጀት ዓመት የቀረበው በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር መጠነኛ ጭማሪ እንዳለው ጠቁመው÷ በጀቱ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሐድጉ÷ በቀጣይ በረቂቅ በጀቱ ላይ ተጨማሪ ውይይት መኖሩን መጠቆማቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።