Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአጂማ- ጫጫ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የውል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንጎለላና ጣራ ወረዳ በአጂማ ወንዝ ላይ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚገነባው አጂማ- ጫጫ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የኮንትራት ውል ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱንም የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ እና የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዘመነ ፀሀይ በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ ስነ ስርዓት ተፈራርመዋል።

በዛሬው እለት የተፈረመው የኮንትራት ውል የፊርማ ስነ-ስርዓት የሎት ሶስት የግድቡ ግንባታ ብቻ ሲሆን፥ በተጨማሪም የሎት አንድና ሁለት የመስኖ መሰረተ ልማት የግንባታ ውል በቀጣይ ጊዜያት የሚፈረም መሆኑን ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ፥ ተቋራጩ የፕሮጀክቱን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በጥራት ገንብቶ እንዲያስረክብ አሳስበዋል።

በተጨማሪም በየደረጃው ያሉት የአማራ ክልል መንግሥት መስተዳድር አካላት ለተቋራጭ ድርጅቱ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ በበኩላቸ፥ው ስራ ተቋራጩ ከአሁን በፊት በክልሉ የገነባቸውን ፕሮጀክቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ፕሮጀክቱን ባለው ልምድና ቁርጠኝነት በታቀደለት ጊዜና በጀት ገንብቶ እንደሚያጠናቅቅ እምነታቸውን ገልፀዋል።

እንዲሁም በተቋራጩ በኩል ጥረት መደረግ እንዳለበት ጠቁመው፥ በኮሚሽኑ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዘመነ ፀሀይ፥ ፕሮጀክቱን ለመገንባት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ግንባታውን በተያዘለት 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ በጥራት አጠናቀው ለማስረከብ እንደሚሰሩም አስታውቅዋል”

አጂማ- ጫጫ የመስኖ ግድብ ግንባታ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ 7000 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

የግድቡ371 ሜትር ርዝመት እና 45 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን፥ 59 ሚሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለውም ተገልጿል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version