አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአዳማ ከተማ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በዛሬው እለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በአዳማ ከተማ የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ በ800 ሚሊየን ብር የተገነቡ 62 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ናቸው በዛሬው እለት የተመረቁት።
በኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ከፍተኛ የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ቡድንም በዛሬው እለት ፕሮጀክቶቹን መርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
በዛሬው እለት ከተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥም የአስፋልት መንገድ፣ የጠጠር መንገድ፣ የጌጠኛ (ኮብል ስቶን) መንገድ እና ድልድዮች ይገኙበታል።
እንዲሁም ግንባታው በ13 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የተካሄደውን የአዳማ ድምፅ ኤፍ ኤም 100 ነጥብ 7 ሬዲዮ ጣቢያንም በዛሬው እለት መርቀው ከፍተዋል።
በተጨማሪም የአዳማ ከተማን የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ለማሻሻል የሚረዱ ፕሮጀክቶች ግንባታ የማስጀመር ስነ ስርዓትም በዛሬው እለት ተካሂዷል።
ግንባታው ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚካሄደው የአዳማ ከተማ ፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይም በኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና በአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ተቀምጧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

