አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዓለም አቀፍ የምርምር ፎረም በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ።
ፎረሙን የአፍሪካ ሕብረት እና ዩኔስኮ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን÷ “የእውቀት ሽግግር ለአፍሪካ መጻኢ ጊዜ” በሚል መሪ ሐሳብ ከመስከረም 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ፎረሙ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ እና የጋራ የምርምር አቅምን በማጎልበት በአፍሪካ እውቀትን ማዕከል ያደረገ ዘላቂ ልማት መፍጠር እና ሁሉን አካታች የሆነ የደቡብ-ለደቡብ የምርምር ትብብሮችን ማጠናከር ላይ ያተኩራል፡፡
በተጨማሪም ብዝሃ የእውቀት ስርዓቶችን በመጠቀም የአፍሪካን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ከአጀንዳ 2063 ማጣጣምና ለአንገብጋቢ የዓለም ፈተናዎች መፍትሔ መስጠት የሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ይመክራል ተብሏል፡፡
የአፍሪካ ምርምር እና ልማት ምኅዳሮች እንዲሁም የእውቀትና ኢኖቬሽን ተደራሽነት ማስፋት በሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በፎረሙ እንደሚዳሰሱ ኢዜአ ዘግቧል፡፡