Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሊተከል ከታቀደው ችግኝ ውስጥ 2 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሊተከል ከታቀደው 5 ቢሊየን ችግኝ ውስጥ 2 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቀረውን 3 ቢሊየን ችግኝ በቀረው ጊዜ ውስጥ ተክሎ ለማጠናቀቅ ይሰራልም ብሏል።

አሁን ላይ ለ5 ቢሊየን ችግኝ መትከያ የሚሆን የጉድጓድ ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

መሬት ውስጥ ያለው እርጥበት ለመጭዎቹ 15 ቀናት ባለበት የሚቆይ በመሆኑ በዚህ ወቅት የሚተከሉ ችግኞች የመጽደቅ መጠናቸው ከፍተኛ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተፈጠረው ግርግር በበቂ ሁኔታ ችግኝ አለመተከሉን የተናገሩት ሚኒስትሩ በመጭዎቹ ቀናት ግን በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያነት በርካታ ችግኞች እንዲተከሉ መታቀዱን አንስተዋል።

የሚተከሉት ችግኞች በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉና በፍጥነት ደርሰው በምግብ ዋስትና የሚስተዋለውን ችግር የመቅረፍ አቅም ያላቸው እንዲሆኑም ጥሪ ቀርቧል።

ህብረተሰቡ የሚያሳርፈው አረንጓዴ አሻራ ከራሱ አልፎ ትውልድን የሚጠቅም መሆኑን በማሰብ በችግኝ ተከላ ላይ እንዲሳተፍም ተጠይቋል።

በዘመን በየነ

Exit mobile version