አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት መሰረት የ5 ሺህ 910 ፓምፕና ጄኔሬተር ርክክብ ተካሄደ፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚኖረውን ጫና ለመቀነስ እንዲያስችል ለመስኖ ዘርፍ ከተመደበው 16 ቢሊየን ብር በተጨማሪ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተመድቧል፡፡
ድጋፉም ለ4 ሺህ አርሶ አደሮች የሚዳረስ ሲሆን ከ23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ግማሽ ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በ22 ከተሞች ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽንን ለማሻሻል የሚውሉ 53 ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችም ለክልሎች ተበርክተዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድጋፉ በሚቀጥለው ዓመት የተሻለ ምርት እንድናገኝ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል ብለዋል፡፡
ክልሎችም የተደረገውን ድጋፍ ለዚህ ስኬት እንዲውል በትጋት እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም ድጋፉን ተጠቅሞው የተሻለ ምርታማነትን ያረጋገጡ ክልሎች የተሻለ ዘመናዊ የመስኖ ግብዓትና ድጋፍ በሽልማት መልክ ይበረከትላቸዋልም ነው ያሉት፡፡
በሀይለኢየሱስ ስዩም

