አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን ከኢንተርኔት ውጪ በመሆን ከዲጂታል ኢኮኖሚው ግዙፍ እድሎች እንዳይገለሉ መረባረብ እንዳለባቸው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ክላቨር ጋቴቴ ጥሪ አቀረቡ፡፡
13ኛው የአፍሪካ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት ፥ መድረኩ በመላው አፍሪካ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካውያን በተመጣጣኝ ዋጋና አስተማማኝ የኢንተርኔት ግንኙነት በማጠናከር የዲጂታል እውቀትና የክህሎት ልማትን በማስተዋወቅ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ግለሰቦችንና የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማጎልበት የሳይበር ደህንነትንና የመረጃ ጥበቃን በማጠናከር አህጉራችንን በዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።
በፓን-አፍሪካ የትብብርና የአንድነት መንፈስ ተግዳሮቶች በማሸነፍ ለሁሉም ብሩህና አካታች የዲጂታል ጊዜን ወደፊት መገንባት እንደሚቻል እምነታቸውን ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ክላቨር ጋቴቴ የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአፍሪካን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በየጊዜው ለሚያሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአፍሪካ ዲጂታል ጉዞ በየዓመቱ 919 ቢሊየን ዶላር በ 856 ሚሊየን ሒሳቦች የሚያስተናግዱ እንደ የሞባይል ገንዘብ ሥርዓቶች ያሉ አዳዲስ ፈጠራዎችን በመጠቀም የዲጂታል ኢኮኖሚውን በማስተናገድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደተግዳሮት ከ800 ሚሊየን በላይ አፍሪካውያን ከኢንተርኔት ውጪ በመሆናቸው ከዲጂታል ኢኮኖሚው ግዙፍ እድሎች የተገለሉ ናቸውም ብለዋል ዋና ጸሃፊው፡፡
ይህንን ለመፍታት አፍሪካውያን በጋራ መረባረብ ይኖርባቸዋል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።