Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ አየር ሃይል 89ኛ የምስረታ በዓል ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ሃይል 89ኛ የምስረታ በዓል በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ተከበረ፡፡

በዓሉን አስመልክቶ በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ አየር ሃይል ፎረም ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እንደተናገሩት፤ የሀገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችል ጠንካራና ዘመኑን የዋጀ አየር ኃይል መገንባት እጅግ አስፈላጊ ነው።

ፎረሙ በዘርፉ ያለውን ልምድ እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረከት ተናግረዋል።

በፎረሙም የአፍሪካ አየር ኃይሎች ማህበር ለመመስረት በሂደቱም ላይ በጋራ ለመስራት ጠንካራ መሰረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።

ለአፍሪካ አየር ኃይሎች መጠናከር እና እድገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ አቻዎቹ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

በተለይም አየር ኃይሉ በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና በሰው ኃይል ልማት ከተለያዩ አቪዬሽን ተቋማትና አየር ኃይሎች ጋር ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

በፎረሙ የአፍሪካ አየር ሃይል መሪዎችና በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት አታሼዎች እየተሳተፉ ሲሆን፥ መድረኩ የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ትብብር መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ሃይል የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች የታጠቀ እና ብቁ የሰው ሃይል ያፈራ መሆኑ በፎረሙ ተነስቷል፡፡

ይህን ይበልጥ በማጠናከርም በ2022/23 ዓ.ም በአፍሪካ ተመራጭ አቪዬሽን ለመሆን እየሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በተለያዩ መርሐ-ግብሮች አየተከበረ የሚገኘው 89ኛው የኢትዮጵያ አየር ሃይል የምስረታ በዓል በቀጣዩ ዓርብ ደግሞ የማጠቃለያ መርሐ-ግብሩ በቢሾፍቱ አየር ሃይል ሐረር ሜዳ ጊቢ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡

በታሪኩ ለገሰ

Exit mobile version