አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የህዝብን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ እየመለሰ ያለው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ፡፡
በወቅታዊ ሃገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ለሶስት ቀናት የተዘጋጀ የደቡብ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ኮንፈረንስ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
አቶ ርስቱ እንዳስታወቁት በህዝቦች ግፊት ዕውን የሆነው የለውጥ ጉዞ ሃገሪቱ ከተጋረጠባት አደጋ ሊታደጋት ችሏል፡፡
ይህም ለውጡ ሠላማዊ በሆነ አካሄድ እንዲጓዝና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በለውጡ ሂደት በተካሄደው ሁለንተናዊ ማሻሻያ ህዝቡን ያማረሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች በመንግስትና ህብረሰተቡ መካከል ፈጥረው የነበሩትን መራራቅ ማረም ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
ለውጥ ያስፈለገው በፊት የተዛነፉና ኢ-ፍትሐዊ የነበሩ አሠራሮችን ለማረም ነው ያሉት አቶ ርስቱ፣ ለውጡ ይመጣብናል ያሉ ኃይሎች ሂደቱን ለማደናቀፍና ህዝቡን መልሶ ለመከራ ለመዳረግ የሚችሉትን ሁሉ ሴራ በመሸረብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እነዚህም ከውስጥና ውጭ ከህዝብ ይልቅ ለግል ጥቅማቸው የሚታትሩ ቡድኖች መሆናቸውን አመልከተው፣ አሁን ላይ የደቡብ ክልል መንግስት ለመፍታት የጀመረውን የአደረጃጀት ጥያቄ ሌላ መልክ ለማስያዝ እየሰሩ ነው ብለዋል አቶ ርስቱ፡፡
ለዚህም በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በተገቢው አለመስራታቸው እንደሆነ ጠቁመው ኮንፈረንሱ ይህንን ለማስተካከል በአመለካከትም ሆነ በተግባር የተዋሃደ የአመራር ቁመና ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

