አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 14 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞችን እንደሚተክል አስታወቀ።
በዚህም ሚኒስቴሩ ዛሬ በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ጋር በመሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 5ሺህ ችግኞችን በመትከል መርሃ ግብሩን አስጀምሯል።
መርሃ ግብሩም “ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን እየተከላከልን አረንጓዴ አሻራችንን እናሳርፍ” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከናወን ነው የተገለጸው።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያን ጨምሮ የስራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህ ወቅት÷መርሃ-ግብሩ አካበቢን ከመጠበቅ በተጓዳኝ ለማህበረሰብ ጤና ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ችግኞች በሚተከሉበት ወቅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ዶክተር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ አመራሮች እና ሰራተኞች የሚተከሉ ችግኞች የአየር ንብረትን በመጠበቅ ለዜጎች ጤና ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመለሰ ምትኩ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

