አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከናወን የቆየው የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የስማርት ቆጣሪዎች ቅየራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ ተግባራዊ እያደረገው በሚገኘው የአድቫንስድ ሜትሪንግ ኢንፍራስትራክቸር ፕሮጀክት ለ39 ሺህ 463 የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የስማርት ቆጣሪዎች ቅየራ አከናውኗል፡፡
መጋቢት 2014 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ 50 ሺህ ለሚሆኑ የኃይል ፍጆታቸው በሠዓት ከ24 ኪሎ ዋት በላይ ለሚጠቀሙ ደንበኞች ነባር የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን በስማርት ሜትር ለመቀየር አቅዶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
በዚህም በሁለት ምዕራፍ የቅየራ ሥራውን ሲያከናከውን መቆየቱን ነው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያስታወቀው፡፡
በዚሁ መሠረት በምዕራፍ አንድ የፕሮጀክቱ ትግበራ 5 ሺህ ነባር ቆጣሪዎች በስማርት ሜትር የተቀየሩ ሲሆን÷ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 34 ሺህ 463 ቆጣሪዎችን መቀየር ተችሏል ብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲታቀድ 50 ሺህ ነባር ቆጣሪዎችን በስማርት ቆጣሪዎች ለመቀየር ታልሞ የነበረ ቢሆንም÷ በኢትዮጵያ ያሉት የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች 39 ሺህ 463 ብቻ በመሆናቸው ለነዚህ ደንበኞች ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል ነው ያለው፡፡
ቀሪዎቹ 10 ሺህ 537 ስማርት ቆጣሪዎች በቀጣይ ከ24 ኪሎ ዋት ሠዓት በላይ አዲስ ኃይል ለሚጠይቁ ደንበኞች አገልግሎት እንደሚውሉም ጠቁሟል፡፡
አዲስ የተቀየሩት ስማርት ቆጣሪዎች ከቆጣሪ ንባብና ከክፍያ ቢል ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረት፣ ደንበኞች ካሉበት ቦታ ሆነው በስልካቸው የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን መከታተል እንዲችሉ ብሎም የኃይል ስርቆትን ለመከላከል የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ሠዓት በተቀየሩት አዲስ ስማርት ቆጣሪዎች አማካኝነት ደንበኞች ትክክለኛ የፍጆታ ክፍያ እንዲከፍሉ እና ተቋሙም ትክክለኛ የኃይል ፍጆታ ሂሳብ እንዲሰበስብ ማድረግ ተችሏል ተብሏል፡፡
በዮሐንስ ደርበው