አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከታሕሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ”ሐይማኖት ለሰላም ለአንድነትና ለመከባበር” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ጉባዔው የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን የሰላም ስምምነት ለማጽናት ብሎም በተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ አካላት የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ገልጿል።
ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይበት፣ አብሮነቱን የሚያጠናክርበትና ለሰላም ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የሚያጎላበትን መድረክ ለማመቻቸት እየሠራ መሆኑን ጉባዔው መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኮንፍረንሱ በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ ስቴዲየሞች የሚካሄድ ሲሆን÷ የመጀመሪያው የሰላም ኮንፍረንስ በድሬዳዋ ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ታሕሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሔድ ተጠቁሟል።