አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ ከቀኑ 5 ሠዓት ከ20 ላይ በፈንታሌ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡
ከአሁን ቀደም የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰትበት በነበረው ፈንታሌ አካባቢ ዛሬም ክስተቱ መስተዋሉን በዩኒቨርሲቲው የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሣይንስ መምህርና ተመራማሪ አታላይ አየለ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡
በሬክተር ስኬልም 4 ነጥብ 3 መመዝገቡን ነው ፕሮፌሠሩ ለፋና ዲጂታል ያረጋገጡት፡፡
በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ትምህርት ቤት ዲን ጌታቸው ገብረ ጻድቃን በበኩላቸው ፥ ፈንታሌ አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪዎች ደውለው ስለሁኔታው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የመሬት መንቀጥቀጡ መከሰቱን እና በሕብረተሰቡ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ነዋሪዎች ነግረውኛል ብለዋል፡፡
የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥም ባለፉት ጊዜያት ሲከሰት ከነበረው ያልበለጠ መሆኑን ነው አቶ ጌታቸው ያስረዱት፡፡
በአፋር ክልል የጋዲ ረሱ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ዓሊ ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ባለፉት ሦስት ቀናትም የመሬት መንቀጥቀጥ መስተዋሉን አስረድተዋል፡፡
በዚህም በፈንታሌ አካባቢ እና አዋሽ 7 ከተማን ጨምሮ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የተመዘገበ ወይም የደረሰ ጉዳት የለም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ በፈንታሌ አካባቢ እና አዋሽ 7 ከተማን ጨምሮ መከሰቱንም አስታውቀዋል፡፡
በአፋር ክልል የጋቢ ረሱ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ዓሊ ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ባለፉት ሦስት ቀናትም የመሬት መንቀጥቀጥ መስተዋሉን አስረድተዋል፡፡
በዚህም በፈንታሌ አካባቢ እና አዋሽ 7 ከተማን ጨምሮ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የተመዘገበ ወይም የደረሰ ጉዳት የለም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው