አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የስንዴ ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት በጅግጅጋ ከተማ ይፋ ተደርጓል።
የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር የሶማሌ ክልል የእርሻ ልማት ቢሮ ሃላፊ አብዲቃድር ኢማን (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።
የስንዴ ልማትን ለማሳደግ ትኩረት ያደረገው ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሶማሌ፣ አሮሚያ፣ አፋርና አማራ ክልሎች በሚገኙ 76 ወረዳዎች የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አብዱልሰመድ አብዶ በበኩላቸው÷የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የስንዴ ልማት ለመደገፍ የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችል የስንዴ ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
አብዲቃድር ኢማን (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ 500 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በሶማሌ ክልል ፋፈን፣ ሸበሌ፣ አፍዴር እና ሊበን ዞኖች በሚገኙ 11 ወረዳዎች እንደሚተገበር ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ ለ5 ዓመት ዓመታት በአራት ክልሎች እንደሚተገበር መጠቆሙንም የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡