አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፋርማሲዩቲካል ኢንቨስትመንት ያለውን የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን ጎብኝተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በጉብኝቱ÷ ባለሀብቶች ወደ ጤናው ዘርፍ ገብተው እውቀትና እና ሀብታቸውን ስራ ላይ ማዋል እንዲችሉ የጤና ሚኒስቴር ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በተገነባው የቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ካለው 279 ሄክታር የለማ መሬት ወስጥ እስካሁን ስራ ላይ የዋለው 39 ሄክታር ገደማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በዘርፉ የተሰማሩ እና ወደ ዘርፉ ለመግባት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የዞኑን ሀገራዊ ተልዕኮ በጋራ እውን እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የሚገኙ መድሃኒት አምራቾች የሀገር ውስጥ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ምርት እያመረቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ይህን ለማሳደግ መንግስት ለሀገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በጤናው ዘርፍ ያለውን የባለሃብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ ተቋማቱ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።