Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ገና በላሊበላ እንደወትሮው ሁሉ በድምቀት ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገና በዓልን እንደወትሮው ሁሉ በላሊበላ ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የዝግጅት ሥራዎችን የሚከውን ኮሚቴ ተደራጅቶ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ሆቴሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ በርካታ እንግዶችን ታሳቢ ያደርገ በቂ ምግብ፣ መጠጥ እና የመኝታ አገልግሎት ዝግጁ  አድርገዋል፤ እንግዶቻቸውንም መቀበል ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል የላሊበላ እና አካባቢዋ ነዋሪ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተለመደ የእንግዳ አቀባበሉን እያደረገ መሆኑን አስረድተው፤ የበዓሉን ማክበሪያ ቦታዎች ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

እንደወትሮው ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንግዳ ወደ ከተማዋ እንደሚመጣ ይጠበቃል፤ እንግዶችም በዓሉን በድምቀት አክብረው እንዲመለሱ የአካባቢው ሕብረተሰብ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የበዓሉን ተጓዦች ብዛት እና ፍላጎት መሠረት በማድረግም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመደበኛው ተጨማሪ በረራዎች ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለተቋማቸው ማረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡

የቱሪስት አስጎብኝ እና የሆቴል ማኅበራትም የበዓሉን እንግዶች ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኝ ማኅበር ሊቀ-መንበር እስታሉ ቀለሙ÷ በተለያየ ጊዜ ጎብኝዎች ወደ ላሊበላ እንደሚመጡ ቢታወቅም በገና ሰሞን ያለው የእንግዶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም 165 አባላት ያሉት ማኅበራቸው በላሊበላ ከተማ የሚገኙትን ከአንድ አለት የተፈለፈሉ ድንቅ አብያተ-ክርስቲያናት ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አሰፋ በበኩላቸው÷ በማኅበሩ ሥር የሚገኙ 52 ሆቴሎች ከሰው ኃይል ጀምሮ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመሥጠትም ሆቴሎች ለእንግዶች በራቸውን ክፍት አድርገው እየጠበቁ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version