አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋቢ ረሱ ዞን በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ30 በላይ የመኖሪያ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸው ነዋሪዎች ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ አስገድዷል፡፡
በአዋሽ 7 ከተማ አሥተዳደር፣ በአዋሽ ፈንታሌ እና አሚባራ ወረዳዎች በሚገኙ የተወሰኑ ቀበሌዎች የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ዓሊ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በዚህም እስከ አሁን በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ እና ዶኾ ቀበሌዎች ከ30 በላይ የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡
ጉዳት በደረሰባቸው እና ሌሎችም ሥጋት ባለባቸው መኖሪያ ቤቶች ያሉ ወገኖችን ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ቀለል ባለ ባህላዊ ቤት እንዲኖሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሰው ላይ የተመዘገበ ጉዳት ባይኖርም÷ በሰብል የተሸፈኑ ማሳዎች እና የመኪና መንገዶች ላይ የከፋም ባይሆን የመሰነጣጠቅ አደጋ መድረሱን አንስተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው