Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያን የማዕድን ጸጋ በመግለጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ አድርጎታል – ሀብታሙ ተገኝ(ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ  ኤም ሲ) የለውጡ መንግሥት ተረስቶ የቆየውን የማዕድን ጸጋ በመግለጥ የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ እንዲሆን ማድረጉን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የማዕድን ሚኒስትር  ሀብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) ገለጹ።

 

ሚኒስትሩ ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፖሊሲና ህግጋት ጀምሮ የዕይታ ለውጥ በማድረግ የሀገርን የማዕድን ጸጋ የማወቅና የመግለጥ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

 

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድም ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል።

 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ደግሞ በወርቅና በሌሎች ማዕድናት የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አንስተው ለአብነትም በወርቅ የወጪ ንግድ ብቻ ለዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ገልጸዋል።

 

በሌላ በኩል መንግሥት የሲሚንቶ ዋጋና የምርት እጥረት ላይ ህዝቡ የሚያነሳውን ቅሬታ ለመፍታት እርምጃ መውሰዱን በማንሳት የግሉን ዘርፍ በማንቀሳቀስ ግዙፍ ፋብሪካዎች በመክፈት እልባት መስጠቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

የሀገር ዕድገት ከማዕድን ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ዘርፉ ለህገወጥነት ተጋላጭ በመሆኑ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት አቋቁሞ እርምጃ እየወሰደ ነው፤ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታትም ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ ነው ብለዋል።

 

ማዕድን ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጠርበትና የዜጎች ህይወት የሚቀየርበት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

 

 

Exit mobile version