Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣የሰላም ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር የችግኝ ተከላ አካሄዱ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 16 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣የሰላም ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር  በዛሬው እለት የችግኝ ተከላ አካሄዱ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች እና አባላት በዛሬው ዕለት  በቢሾፍቱ ከተማ  የችግኝ ተክላ አካሂደዋል፡፡

በችግኝ ተከላ ስነ ስራዓቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ መሳተፋቸው ተገልጿል ፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በመርሀ ግብሩ ላይ ÷ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው የውኃ ሙሌት መረኃ ግብር ተጠናቆ፤ ዛሬ ደግሞ የችግኝ ተከላ ማካሄዳችን በአንድ በኩል ነገ ለምንፈልገው ዘላቂ ልማት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ  ነው ብለዋል።

ምክትል አፈ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በበኩላቸው÷የዛሬው ችግኝ ተከላ እና የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት  ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በዘንድሮው የአረንጎዴ አሻራ ፕሮግራም ስምንት ሺህ ችግኞችን ለመትከል ያቀደ ሲሆን÷ እስካሁን አራት ሺህ ችግኞችን መትከሉን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር በዚህ ዓመት በሚካሄደው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ማቀዱ ተገልጿል።

በዛሬው እለት የሚኒስቴሩ አመራሮችና ሰራተኞች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 01 በረጲ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የችግኝ ተከላ  አካሄደዋል።

የሰላም ሚኒስትር  ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመርሀ ግብሩ ላይ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው÷በትላንተናው ዕለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ደስታውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው ገልፀዋል ፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር  ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በዛሬው እለት ከቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች  እና መምህራን ጋር የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

የችግኝ ተከላው የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ አመት የውሃ ሙሌት በተጠናቀቀ ማግስት መደረጉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር መሆኑን በመተማመን ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

አያይዘውም የአባይ ውሃ ለም አፈርን ይዞ መሄዱን እያስተዋልን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የችግኝ ተከላው አስተዋፅኦው የጎላ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ከ37ሚሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version