Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማካሄድ ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የተፈጥሮ ሚዛንን ለማስጠበቅ እና የአፈር ለምነትን ለማሳደግ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ሚናው ጉልህ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ ለሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራም አስፈላጊው የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራውን በስኬት ለማከናወን 9 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ አንስተዋል።

በዚህም 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ነው ያስረዱት።

ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው የሚውሉ የቁፋሮና ሌሎች መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው÷ለግብርና ባለሞያዎች ሥልጠና መሰጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው ተፋሰሶች ተለይተዋል ያሉት አቶ አሊያስ÷በመርሐ ግብሩ 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ሥራ እንደሚሰራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በመጪው ጥር 14 ቀን በይፋ በሚጀምረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የክልሉ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version