አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በግድቡ ላይ የነበራቸውን ተስፋ ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡
የመጀመሪያው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን በመገናኛ ብዙሃን መከታተላቸውን አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡
በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ዕጩ ተመራቂ ገብሩ ካሕሳይ÷ የግድቡ የውሃ ሙሌት በጉጉት ይጠብቀው ስለነበር ዜናው መስማቱን ተከትሎ ደስታ እንደፈጠረበት ገልጿል፡፡
የግድቡ ውኃ ሙሌት የመጀመሪያ ዙር መጠናቀቅ በራሳችን አቅምና ገንዘብ የግድቡ ግንባታ እውን ማድረግ እንደምንችል በተግባር ያሳየ ነው ብሏል ።
ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ጥቅም እስኪቀየር ድረስ መንግስትና ህዝብ ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት እተማመናለሁ የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
የመጀመሪያው ዙር የውኃ ሙሌት ራሱን የቻለ ውጤት ነው ያሉት ደግሞ በህዳሴ ግድቡ ላይ ለዓመታት ጥናታዊ ጽሁፍ በማቅረብ የሚታወቁት የጂኦግራፊ ምሁር ብርሃኑ በላቸው ናቸው፡፡
የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ የሚበረታታ ውጤት መሆኑን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ÷ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም መስራት የሚችሉ መሆናቸው በድጋሚ ለአለም ማህበረሰብ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የአደረጃጀትና ህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ሃይለኪሮስ ጠዓመ በበኩላቸው÷ የመጀመሪያው ሙሌት መጠናቀቅ ህዝቡ በግድቡ ግንባታ ያሳየው ተሳትፎ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ የታየውን የህዝቡ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር ማስተባበሪያው አስፈላጊውን የማነሳሳት ስራ የሚያከናውን መሆኑን አቶ ሃይለኪሮስ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

