Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች በቻይና ከተሞች ባደረጉት ጉብኝት ለኮሪደር ልማት ግብዓት የሚሆኑ ልምዶች መቅሰማቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቻይና ናንጂን እና በያንጆ ከተሞች ባደረጉት ጉብኝት በመዲናዋ እየተካሄደ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ግብዓት የሚሆኑ ልምዶች መቅሰማቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በቻይና ጂያንግሱ በነበረን የሁለት ቀን ጉብኝት ከያንጆ ከተማ የሲፒሲ ሴክሬተሪ ከሆኑት ዋንግ ጅንጂአን ጋር ተገናኝተን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ለይ በትብብር ለመስራት ተወያይተናል ብለዋል።

በተጨሜሪም ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና ቴክኒክ ትብብር ጉዳዮች ሊቀ መንበር ሶንግ ቺንቦ ጋር በመገናኘት በትብብር አቅጣጫዎች እና ዘርፎች ዙሪያ መወያታቸውንና በቀጣይ አብሮ ለመስራት መግባባታቸውን አመላክተዋል።

በናንጂን እና በያንጆ ከተሞች ባደረግነው ጉብኝት በከተማችን እየተካሄደ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ግብዓት የሚሆኑ ልምዶች ቀስመናልም ነው ያሉት ከንቲባዋ።

ትላልቅ የወንዝ ዳርቻ እና የከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶችን፣ የመኖሪያ ቤቶችን በስፋት ለመገንባት ለያዝነው እቅድ ግብአት የሚሆኑ፣ በፍጥነት እና በጥራት ለማከናወን የሚያስችሉ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም በጥራት እና ስፋት እየተተገበሩ ያሉትን የከተማ ግብርና ስራዎችን ጎብኝተናል ሲሉም ገልጸዋል።

በጉብኝታችን የተመለከትነው እና ለሀገራችን ተስማሚ የሆኑትን የግንባታ የቴክኖሎጂዎች እና የእውቀት ሽግግር ላይ ለመስራት ተግባብተናል ሲሉም አክለዋል።

Exit mobile version