አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) ቻይና አሜሪካ በቼንግዱ የሚገኘውን ቆንስላዋን እንድትዘጋ አዘዘች፡፡
የአሁኑ የትዕዛዝ ውሳኔ አሜሪካ ከትናንት በስቲያ በሂውስተን የሚገኘው የቻይና ቆንስላ እንዲዘጋ ማዘዟን ተከትሎ የተወሰደ የአፀፋ እርምጃ ነው ተብሏል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ቆንስላው በ72 ሰአታት ውስጥ እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፏል ነው የተባለው፡፡
ከውሳኔው በኋላ የሃገሪቱ የአክሲዮን ገበያ እና የቻይና መገበያያ ገንዘብ ከዶላር አንጻር ያለው ምንዛሬ ማሽቆልቆላቸው ነው የተነገረው፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቻይና የአሜሪካ ኤምባሲ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
ቤጂንግ ዋሽንግተን ረቡዕ ዕለት የወሰደችውን እርምጃ በማውገዝ የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃ ነበር፡፡
ውሳኔዋንም ከዓለም አቀፉ ህግ እና ከአሜሪካ ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንጻር እንድትሽርም መጠየቋ ይታወሳል፡፡
የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በተለይም በዚህ አመት ፍጥጫ በዝቶበታል፡፡
የንግድ እና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች፣ ኮሮና ቫይረስ፣ የቻይና በደቡባዊ የቻይና ባህር የምታደርገው መስፋፋት እና የሆንግ ኮንግ ጉዳይ ሃገራቱ እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
የአሁኑ የቻይና ውሳኔም የሃገራቱን ግንኙነት ወደባሰ ፍጥጫ እንዳያስገባው ተሰግቷል፡፡
ምንጭ፡- ሬውተርስ

