አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) በመኸር እርሻው 7 ነጥብ 75 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በበጀት አመቱ የእርሻ ወቅት 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በበልግና በመኸር እርሻው 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ ከ375 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ነው የተናገሩት።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅዕኖን በመቋቋም የግብርና ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርም ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ እንዲቀርብ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ከምርጥ ዘር አቅርቦት አንጻር የአርሶ አደሩን ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ማሟላት ባይቻልም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አቅርቦት እንዳለም አውስተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሁለት አይነት የአፈር ማዳበሪያ ብቻ ይቀርብ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኢሳያስ፤ እንደየአፈሩ ተስማሚነት ሰባት ዓይነት ንጥረ ነገር ያለው የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን ገልጸዋል።
የአፈር ለምነትን ከመጠበቅ አንጻርም 62 ሺህ ሄክታር መሬት ከአሲዳማነት ለማከም ታቅዶ 14 ሺህ ሄክታር መሬት በኖራ ታክሟል ነው ያሉት።
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ውጤት እያመጣ የሚገኘው የኩታገጠም እርሻ አሰራር በዚህ ዓመት በ400 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በመኸር እርሻው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ አርሶ አደሩ መሬቱን በማጠንፈፍ በተገኘው አጋጣሚ በተለያዩ ሰብሎች እንዲሸፍንም ጥሪ አቅርበዋል።

