Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሃገር አቀፍ የምርት ጥራት ደረጃ ለማሳደግ የስምምነት ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ መካከል ሃገር አቀፍ የምርት ጥራት ደረጃን ለማሳደግ የሚረዳ የስምምነት ሰነድ ተፈረመ ፡፡

ስምምነቱ ለሀገር ውስጥና ለወጪ ንግድ የሚቀርብ የጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ ማር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

የንግድ ጥራትና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት÷ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው ለገበያ እንዲቀርቡ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ እስካሁን ድረስ የምርት ጥራት ደረጃ የወጣላቸው 11 ሺህ 800፣ በአስገዳጅ ደረጃ 170 የወጣላቸው ምርቶች የሚገኙ ሲሆን በዋናነት በጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ ማርና አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የምርት ጥራት ደረጃ ለማውጣት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ስምምነቱ በዋናነት የምርት ጥራት ደረጃ የወጣለቸው ከውጭ የሚገቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚያግዝ መናገራቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version