አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ክልል አቀፍ የባህል ፌስቲቫል በጎንደር ከተማ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ፌስቲቫሉ ”ድንቅ ምድር ድንቅ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ በጎንደር ከተማ ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ይካሄዳል።
በዓሉን በስኬት ለማክበር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ዓብይና ንዑስ ኮሚቴ ተቋቋሞ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ስራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።
ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተወጣጡና አካባቢያቸውን የሚወክሉ የባህል ቡድኖች በሁነቱ ይሳተፋሉ።
ወሎ፣ ላሊበላ፣ ግሽ ዓባይና ፋሲለደስ የባህል ቡድኖች ከዓመታት በኋላ በፌስቲቫሉ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
በተጨማሪም በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል።
ባለፉት 15 ተከታይ ዓመታት የተከበሩ መሰል በዓላት የክልሉን የቱሪዝም ሃብት ከማስተዋወቅ ባለፈ ለእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል ነው የተባለዉ።
ዘንድሮ የሚካሄደው የባህና የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ዋና ዓለማ የክልሉን ኪነ-ጥበብ ለማነቃቃት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
በምናለ አየነው