Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ በተራራ ልማት ኢኒሼቲቭ 4 ሺህ 350 ሔክታር እየለማ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ የተራራ ልማት ኢኒሼቲቭ 4 ሺህ 350 ሔክታር የተራቆቱ ተራሮችን መልሶ የማልማት ሥራ እየተከናነወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከመደበኛ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በተጨማሪ ርዕሰ መሥተዳድሩ ለተራራ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት “በአንድ ዞን አንድ ተራራ መልሶ የማልማት” ክልላዊ ኢኒሼቲቭ ማስተዋወቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አስታወሷል፡፡

በዚህም በዞኖቹ የሚለሙ የተራቆቱ ተራሮች ካርታን ለየዞኑ በማስረከብ መልሶ የማልማት ሥራ ማስጀመራቸውን መረጃው አመላክቷል፡፡

ይህን ተከትሎም በዞኖቹ የሚገኝ 4 ሺህ 350 ሔክታር የተራቆቱ ተራሮች ሥነ-ምኅዳር በደንና የፍራፍሬ ችግኞች መልሶ የማልማት ተግባር ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀትም የተራሮች መሠረታዊ መረጃዎች በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ የመሰብሰብና የማጠናቀር ሥራ እየተተገበረ ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የተራራ ልማትና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች÷ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን ለመከላከል፣ የውኃና ብዝኃ ሕይወት ሀብትን ለመጠበቅ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ከባቢና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጎላ ሚና ስላላቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ተብሏል፡፡

Exit mobile version