Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በፈጠራ የተሞላ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዕውቀት እና በፈጠራ የተሞላ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሠራ ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ጋር በጋራ ለስድስት ወራት ያሰለጠናቸውን 12 ስታርታፖች ዕውቅና ሰጥቷል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ዴዔታው የስታርታፖች ዘርፍ የሀገርን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዕድሉን በአግባቡ የተጠቀሙ ወጣቶች ችግር ፈች የፈጠራ ውጤቶችን ከማሳየት ጀምሮ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቀጣይ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና የመሰረተ ልማት ግንባታ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

የኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር አስተባባሪና ኤክስፐርት ቾይ ያንግ ጁን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ በዘርፉ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ የፕሮጀክት አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሁለት ስታርታፖች የ10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በብርሃን ደሳለኝ እና ሳሙኤል ወርቃየሁ

Exit mobile version