አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት ከተራ በዓል አከባበር ልዩ የአድናቆት ስሜት እንደፈጠረባቸው ክብረ በዓሉን በአዲስ አበባ የተከታተሉ የተለያዩ ሀገራት ጎብኝዎች ገለጹ።
ፈረንሳውያኑ ጎብኝዎች ማዲ ሴራውልት፣ ባፕቲስቴ ሜካሪ እና ዮዮ ሜካሪ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶችን እና ክዋኔዎችን ለምዕት ዓመታት ጠብቃ ለትውልድ በማስተላለፏ እንደ ጥምቀት ያሉ ክብረ በዓላትን ለዓለም ማበርከት አስችሏታል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የእንግዳ አቀባበል እና በከተማዋ ገጽታ መደሰታቸውን ገልጸው መዲናዋን ለዚህ መሰል ማራኪ ሁነቶች ተመራጭ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በዓሉ ላይ ባስተዋሏቸው ባህላዊ አልባሳት፣ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች እና ህብረ ዝማሬዎች መደነቃቸውን ጠቁመው ይህም የሀገሪቱን ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶችን የበለጠ ለማወቅ እንዳነሳሳቸው እና ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን ለመጎብኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ጣልያውያኑ ኤልኖራ ሎሊ እና ጆርጂያ ሪቺ በበኩላቸው የጥምቀት ከተራን በዓል አስደናቂ ሃይማኖታዊ የአደባባይ ሁነት ሲሉ ገልጸውታል።
የህብረ ዝማሬዎቹ ዜማ፣ የአልባሳቱ ህብረ ቀለማት፣ የዘማርያኑ ቅንጅት እና እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ሃይማኖታዊ የዜማ መሳሪዎች ውህደት ልዩ የአግራሞት ስሜት ፈጥሮብናል ብለዋል። ኢትዮጵያ ዓለም ሊያውቃቸው የሚገቡ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች እንዳሏት እምነታቸው እንደሆነ የገለጹት ጎብኝዎቹ በበዓሉ ላይ ያስተዋሉትን ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በሚያገኙት አጋጣሚ እንደሚያስተዋውቁ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ