አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋይዳ መታወቂያ መኖር በኢትዮጵያ የዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማትን በፍጥነት ለመተግበር መልካም እድል ይሰጣል ሲሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት አማካኝነት የተዘጋጀ እና በዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች ብለዋል።
መንግሥት ለዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው÷ በተለይ የፋይዳ መታወቂያ መኖር በኢትዮጵያ የዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማትን በፍጥነት ለመተግበር መልካም እድል የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የቶኒ ብሌየር ከፍተኛ አማካሪ እና የቀድሞ የሕንድ ኤሌክትሮኒክ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ኢንተርፕርነርሺፕ ሚኒስትር ራጂቭ ቻንድራሴክሃር÷ ሕንድ የፐብሊክ መሰረተ ልማት ላይ በመመስረት ስላስመዘገበችው አስደናቂ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውጤት አስረድተዋል።
የቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማለዳ ብስራት÷ ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሚሽንን እውን ለማድረግ ከመንግስት ጋር በትብብር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ መንግስት የሚያደርጋቸውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ተግባራት እንደሚደግፍ ማረጋገጣቸውን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከዲጂታል መታወቂያ ጽሕፈት ቤት፣ ከኢንፎሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከኢቲስዊች የተውጣጡ የሥራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።