አዲስ አበባ፣ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥምቀት በዓል የሥርቆት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ከ20 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የጥምቀት በዓል የሚመለከታቸው አካላት ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተባብረው በመሥራታቸው በድምቀትተከብሮ መጠናቀቁን ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ገልጿል፡፡
ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ባዘጋጀው የፀጥታ ዕቅድ እየተመራ በዓሉ በተከበረባቸው የከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሕዝቡን ሠላምና ደህንነት በማስቀደም ከከተራ ዕለት ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ ተግባራትን ማከናወኑ ተመላክቷል፡፡
ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ በማቋቋም የምርመራና የክትትል ቡድን በማዋቀር ከፍትሕ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተከናወነ ተግባር ወንጀልንና የወንጀል ስጋቶችን መቆጣጠር መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የስርቆት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ነው ተብሏል፡፡
ከተያዙት መካከልም የተወሰኑት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡