Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል።

ካቢኔው ዘመናዊ የአሶሳ ከተማ አስፓልት የመንገድ ዳር መብራት ተከላን በተመለከተ ተወያይቷል።

የአሶሳ ከተማ እድገት ጋር ተያይዞ እየተከናወነ የሚገኘው የመንገድ መሰረተ ልማት ስራ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ከተማን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ ከሚገኙ መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት በነቃ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወነ በመሆኑ ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ዳር መብራት መትከል እንደሚያስፈልግ ካቢኔው መክሯል፡፡

የከተማዋን እድገት የሚመጥን ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ ማሟላት እንደሚገባ የገለጸው ካቢኔው÷ በጥራትና በፍጥነት ተከላው ተጠናቆ ለህዝቡ አገልግሎት አገልግሎት እንዲሰጥ በልዩ ሁኔታ የቅርብ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

የመንገድ ዳር መብራት ተከላው በውስጡ ለተገልጋዮች ቻርጅ ማድረጊያ፣ የኔትወርክ አገልግሎት፣ ካሜራና ሌሎች ተያያዥ ዘመናዊ የቴክኖሎጂዎችን በውስጡ አሟልቶ እንደሚይዝ ተጠቅሷል።

የክልሉ መንግስት ካቢኔም የመንገድ ዳር መብራቱ በአሶሳ ከተማ በተመረጡ ቦታዎች እንዲተከል እና ሙሉ ስራውንም ዳቡስ ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራውን እንዲያከናውን ወስኗል።

ካቢኔው በዚህና በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አስቸኳይ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version