Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በነበረው የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እያቀረበ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በነበረው የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ 7 ሺህ 800 ሰዎች የዕለት ደራሽ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታወቁ።

ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ዳመነ ዳሮታ ኮሚሽኑ ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ሕልፈት በኋላ በነበረው የፀጥታ ችግር በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያቀረበ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ ድጋፉን እያደረገ ያለው ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎችን ሲሆን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እስከ 10ሺህ የሚደርሱትን ወገኖች ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኮቪድ 19፣ በግጭቶችና ከአንበጣ መንጋ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ችግሮች ዕርዳታውን ለማቅረብ ባለብዙ ዘርፍ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን እያደረገ መሆኑን አቶ ዳመነ አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው የበልግ ወቅት ባልተጠበቀ ሁኔታ ጉዳት ለደረሰባቸው 301 ሺህ ሰዎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ መስጠቱን አስታውቀዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የክምችት አቅምን ለማሳደግ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

Exit mobile version