Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለጃፓን ኢንቨስተሮች የተመቸች በመሆኗ በርካታ ኩባንያዎች እየተሳተፉ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለጃፓን ኢንቨስተሮች የተመቸች መዳረሻ በመሆኗ በርካታ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እየተሳተፉ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖሪ ገለጹ።

ከ50 በላይ ከጃፓን የመጡ የቢዝነስ ልዑካን የተሳተፉበት የኢትዮ-ጃፓን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ተጀምሯል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ እና የህግ አሰራሮች የሚያበረታቱ በመሆኑ የጃፓን ኢንቨስተሮች ጋር የኢትዮጵያ መንግስት በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በመክፈቻው፤ ኢትዮጵያ እና ጃፓን ጠንካራ እና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየሙ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እና አቅሞችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያግዛል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የጃፓን ኩባንያዎች በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት እና በመንግሥት በኩል ያሉ ማበረታቻዎች ይበልጥ ምቹ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የጋራ እድሎችን በመጠቀም የቢዝነስ እና የንግድ ግንኙነትን ይበልጥ ማላቅ እንደሚገባም መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ፤ የሀገራቱን የኢንቨስትመንት እና የቢዝነስ ግንኘነት ይበልጥ ለማሳደግ በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖሪ ኢትዮጵያ ለጃፓን ኢንቨስተሮች የተመቸች መዳረሻ በመሆኗ በርካታ ኩባንያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት ያላት ተስፋ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት ዘርፍ በግብርና ያሉ እድሎች ለዘላቂ እድገት እና ትብብር መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

Exit mobile version