አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለገቡ ታጣቂዎች አባ ገዳዎች ምስጋና አቀረቡ።
በክልሉ ይንቀሳቀሱ ለነበሩና የሰላም አማራጭን ለተቀበሉ ታጣቂዎች እውቅና እና ምስጋና የሚያቀርብ መርሐ-ግብ ተካሂዷል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙ አባ ገዳዎች እንደገጹት፤ ታጣቂዎቹ ለወሰኑት ትክክለኛ ውሳኔ እና ለተከተሉት የሰላም መንገድ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ሰላምን ለማጽናት እና የሃሳብ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ሲወስዱ ቆይተዋል።
በዚህም ሀገራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱም ነው የተገለጸው፡፡
ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት የፈጸሙት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር አቶ ሰኚ ነጋሳ፤ ታጣቂዎቹ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡